OlongoAfrica Multilingual Anthology
Illustration for የፀሀይ ግርዶሽ
Illustrations by Gemini

የፀሀይ ግርዶሽ

by Ìfẹ́olúwa Adéníyì

(First published as Eclipse by Ìfẹ́olúwa Adéníyì in OlongoAfrica, 2024)
Translated to Amharic by Tesfaye Kirubel

Listen to the Narration

Narrated in Amharic by Natahim Addis.


በአስር አመት ውስጥ ስለታየው ትልቁ የፀሀይ ግርዶሽ

አያታችን የቤተሰቡን አባላት ድምፁን ከፍ አድርጎ በመጣራት ፣ “ጨረቃ እንዴት ፀሀይን እንደምትጋርድ ኑና ተመልከቱ!” በማለት ከቤታችን ጓሮ ወደሚገኘው ቦታ ጠራን። እጄታው የወርቅ ልጥፍ የሆነውን ከዘራውን ይዞ የሚወዳት ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሏል። ያደረጋትን በሀኪም የታዘዘለትን ጥቁር መነፅር ድሮ ይነዳት ከነበረችው ማርሴዲስ መኪና ጋር እያወዳደረ፣ “ይህ መነፅር እኮ የዚህን መኪና ግማሽ ዋጋ ያወጣል!” እያለ ሁልጊዜ ይነግረናል። ባለፈው ዓመት አያቴ ከባድ የአይን ህመም ደርሶበት የአይን ብርሀኑን መልሶ ስለማግኘቱ ዶክተሮች እራሱ የተጠራጠርሩበትን አስቸጋሪ የአይን ቀዶ ጥገና አድርጎ ነበር። ቀዶ ጥገናው በሰላም መጠናቀቅ ቻለ። የሚገርመው ነገር አያቴ በቀዶ ጥገናው ወቅት ተሰጥቶት ከነበረው ማደንዘዣ የነቃበት ቀን ከ90ኛ አመት የልደት በዓሉ ጋር ተገጣጥሞ ነበር። የአያቴ ከቀዶ ጥገናው ማገገም እና የልደት በዓሉ መገጣጠምን ተከትሎ ያልጨረሰው አንድ የቤት ስራ ነበር። የአይን ብርሃኑን መልሶ እንዲያገኝ የረዱትን ሁለት የቀዶ ጥገና ሀኪሞች ጠርቶ በሚገባ ምስጋና አቀረበላቸው።

አያቴ ግርዶሹን እንድናይ በጋበዘን ጓሮ ባለው የመሰብሰቢያ ስፍራ ሰው ተገኝቷል። አባቴ በጠቆሩ ከንፈሮቹ ሲጋራውን እያጨሰ በአያቴ ግራ ቆሟል። የሚገርመው እዛው አያቴ ጎን ቆሞ እያየሁት ሶስተኛ ተከታታይ ሲጋራውን እያጨሰ ነው። አባቴ የተሸበሸበ ግንባሩን ለመሸፈን ጭንቅላቱ ላይ የቤዝ ቦል ተጨዋቾች ኮፍያ አድርጓል። ነገር ግን ኮፍያው ወደጎን ከመንሻፈፉ የተነሳ ፊቱን በግልፅ ያሳያል። ለሚያየው ሰው እንቅልፉን ሳይጨርስ ሲጠጣ ያደረ ሰው ነው የሚመስለው። አባቴ በአንድ እጁ ጥብቅ አድርጎ የያዛት አደል በየትኛውም የቤተሰብ ስብሰባ ወቅት ምንጊዜም ከጎኑ አትለይም። ባለፉት አመታት አንድ የሚያስጨንቃት ከባድ ነገር እንዳለ እና ህክምና እየተከታተለች እንደሆነ ሁሉም ይጠረጥራል። አሁን አሁንማ እንደዚህ እስካሁን አብሮ ጥብቅ ያደረጋቸው ፍቅር ሳይሆን አይቀርም እያልን እኛ ራሱ ማሰብ ጀምረናል። አባቴ ፊቱን ለመሸፈን ኮፍያ እንዳደረገው ሁሉ አደልም ጥቁር መነፅር ብታደርግም ፣ አይኗን መሸፈኗ አያታችን ሊያሳየን ከሰበሰብን ግርዶሽ ጋር ምንም እንደማይገናኝ ሁላችንም እናውቃለን። ከአደል ጀርባ ቆሞ ያለው ደግሞ ፓፓ ዲ ነው። ፓፓ ዲ የክርስትና አባቴ እና የአባቴ የቅርብ ጓደኛ ነው። እንደዛሬው ሁሉ ምንጊዜም በቤተሰብ ስብሰባ ላይ ቀርቶ አያውቅም። ሲጀመር እንዴት ሊቀር ይችላል? አሁን በህይወት የሌለችው ሴት አያቴ አባዬ እና ፓፓ ዲ ገና በሆድ ውስጥ ሲፀነሱ ጀምሮ እንደሚተዋወቁ ያክል ናቸው እያለች ስለሁለቱ ትነግረን ነበር። ሴት አያቴ እና የፓፓ ዲ እናት የወሊድ ክትትል በሚያደርጉበት ጊዜ ነበር በአንድ ክሊኒክ ውስጥ የተዋወቁት። የሚገርመው ደግሞ አባዬ እና ፓፓ ዲ በአንድ ቀን እንደተወለዱ ትነግረን ነበር።

“አያችሁ? ዝምብላችሁ ተመልከቱ ፣ ጨረቃዋ አሁን ፀሀይን አቋርጣ ታልፋለች” አለ አያቴ። ልክ አያቴ እንደዚህ ብሎ ሲናገር፣ ወንድሜ ኦሱፓ የደስታ የሚመስል ድምፅ አወጥቶ ሳቀ። ኦሶፓ ግርዶሹን ለብቻው ተስተካክሎ ለማየት እንዲመቸው በውሃ የተሞላ ሳህን ይዞ ለብቻው ይሯሯጣል።ልክ ገና መሰብሰብ ስንጀምር ጨረቃ በፀሀይ እና በመሬት መካከል በምትሆንበት ወቅት አይናቸውን አንስተው በቀጥታ እንዳይመለቱ ባዮሎጂ አስተማሪያቸው እንዳሳሰባቸው በመናገር “ወየሁላችው አለበለዚያ የአይን ብርሀናችሁን ታጣላችሁ! ግርዶሹን መመልከት ከፈለጋችሁ በውሃ ውስጥ ነው መመልከት የሚኖርባችሁ” እያለ ኦሱፓ ያስጠነቅቃል።

ኦሱፓ ገና ግርዶሹም ሆነ ምኑም ሳይጀመር አያቴ እቃዎቹን የሚያስቀምጥበት ቤት ውስጥ እየተሯሯጠ ያልተበሳ የውሀ መያዣ ሰሀን እየፈለገ ሲሯሯጥ ነበር። የውሃ መያዣ ሰሀኖቹን ፈልጎ ለማግኘት የሚያደርገውን ግርግር ያየ ሰው ኦሱፓ በጣም ደስ እንዳለው መገመት አይከብደውም። በተለይ ደግሞ ያገኛቸው የተበሱ የውሃ መያዣ ሰሃኖች በውሀ ውስጥ የሚያልፈውን ነፀብራቅ ሊያሳዩት ስለማይችሉ ሌላ ያልተበሳ ሰሀን ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት ማየት ያስደስታልል። ኦሱፓ እድሜው ገና አስር ዓመት ነው። እሱ በተወለደበት ዓመት ማለትም ከተወለደ ከስድስት ቀን በኋላ በከፊል የፀሀይ ግርዶሽ ታይቶ ነበር። የሚገርመው ደግሞ እንደአጋጣሚ ሆኖ የዚያኑ ቀን ነበር ስም የወጣለት። አያቴ የፀሀይ ግርዶሹን አይቶ ነበር ኦሱፓ ብሎ ስም ያወጣለት።

አያቶቼ እና የፀሃይ ግርዶሽ የተለየ ግንኙነት ያላቸው ይመስለኛል። የሚገርመው የኦሱፓ ስም በወጣበት ቀን አያቶቼ ጓደኞቻቸውን እና ቤተሰብ ጠርተው የኦሱፓን ግርዶሽ በታየበት ቀን መወለድ በአለም ታሪክ ላይ ወደፊት ሊፈጠር ላለው ነገር ማሳያ እንደሆነና የእሱን መወለድ ከተፈጥሮ ድንቅ ስራ ጋር አያይዘው ይናገሩ ነበር ነበር። አያቶቼ ይህን በሚናገሩበት ወቅት እማዬ እና አባዬ በቦታው ነበሩ። አልረሳውም ፤ እኔ እራሱ የዚያን ጊዜ ትንሽዬ የስድስት አመት ሴት ልጅ ነበርኩ።

እኔ ደግሞ በልጅነቴ ከእኛ ቤት ቀጥሎ ካለው ቤት ውስጥ ይኖር ከነበረው ታጁ ጋር በልጅነቴ እየተጫወጥኩ ማደግ በመቻሌ በጣም እድለኛ ነኝ። የግርዶሽ ቀን ሆነም አልሆነም ቤተሰብ የሚሰበሰብበት ቀን ብቸኛ ልጅ ስለሆንኩ አያቴ ቤት መሄድ ለኔ ከምንም በላይ የሚያስደስተኝ ነገር ነበር። በድሮ ጊዜ እኔ እና ታጁ ከእኛ ቤት ጓሮ በሚገኘው ቦታ ላበባለ ሶስት እግር የቴኒስ መጫወቻ ጠረጴዛ ላይ ትንንሽ ጠጠር ድንጋዮችን እንደ ቴኒስ መጫወቻ ኳሶች አድርገን ጠረጴዛው ላይ እያነጠርን እንጫወት ነበር።

እስካሁን ድረስ ያንን ከታጁ ጋር ስንጫወትበት የነበረበትንን ቀን አልረሳውም። ምክንያቱም እማዬ እና አባዬ አብረው በአንድ ቤት ውስጥ የነበሩበት የመጨረሻው ምሽት ነበር። በማግስቱ ጠዋት ላይ ነበረ እማዬ ጥላን የሄደችው። እኔም ከአያቶቼ ለምዶብኝ ነው መሰለኝ የእናቴን ከአባቴ ጋር ተጣልቶ መውጣት ከግርዶሽ መታየት ጋር የማያይዘው። እናቴ ከአባቴ ጋር ተጣልታ ከወጣች ከሁለት ወራት በኋላ እኔን ብላ ወደ ቤት ተመልሳ መጥታ ነበር።

እኔ የተሰበሰቡትን ሰዎች እያየሁ በሀሳብ ሄጄ ሳለ “ሁላችውም ውጡ እና ተመልከቱ! ብዙ እኮ አይቆይም ቶሎ ነው የሚያልፈው” ብሎ አያቴ ሲናገር ከገባሁበት ሀሳብ ባነንኩ። እናቴም አያቴ ይህን ሲናገር ከቤት ውስጥ ወጥታ ሁሉም እዚያ አካባቢ የተሰበሰበውን ሰው አልፋ ወደተሰበሰብንበት ስፍራ ተቀላቀለችን። በደንብ እንዲታያትም ይመስለኛል ከእኛ ትንሽ እራቅ ብላ ቆመች።

ኦሱፓ አይኑን ፍጥጥ አድርጎ የጨረቃዋን ነፀብራቅ እየተመለከተ “ወይኔ፣ በሰሀን ውስጥ ትልቅ ሆኖ ነው የሚታየው!!” ብሎ እንደፍራቻም እንደማልቀስም አደረገው።

ልክ ኦሱፓ እንዲህ እያለ ለማለቃቀስ ሲያቃጣቅ እናቱ አደል ፣ “ሽሽሽ... እስኪ ዝም በል ድምፅህን ቀንስ” አለችው። አደል ይህን ተናግራ ሳትጨርስ ወዲያውኑ ፀሀይ ጠልቃ ሰማዩ ጨለማ ሆነ። ልክ ሁሉም ሲጠብቁት የነበረው ሰዓት እንደደረሰ አያቴ ሲያውቅ በሁኔታው በመደነቅ ስሜት “ተመልከቱ!!” እያለ ሳቅ አለ።

ይህ ግርዶሽ እየታየ ባለበት ጊዜ ፓፓ ዲ በእጆቹ የአደልን ጀርባ (ከባድ ቀን ስላሳለፈች ሊሆን ይችላል አላውቅም ብቻ) እንደማጽናናት ነገር ጀርባዋን ይነካካታል። ዛሬ ቀኑ ከባድ ነበር፤ እሱ ብቻ ሳይሆን ፀሀዩ በጣም ሀይለኛ ከመሆኑ የተነሳ በጣም ያቃጥል ነበር።

ሁሉም የተጠራው ሰው የፀሀይ ግርዶሹ ከመከሰቱ ከሰዓታት በፊት ነበር የተሰባሰበው። ይህ የቤተሰብ ስብሰባ ለአደል ከባድ እንደሚሆን መገመት አይከብድም። የመጣውን ሰው ማስተናገድ እንዲሁም የቤቱን ስራ ማከናወን ትልቅ ስራ ነው። ፓፓ ዲም ምን ያህል እገዛ እና እርዳታ እንደሚያስፈልጋት ስላወቀ ይመስለኛል ሊያጽናናት የሞከረው።

ወድያው ብርሀን ቀስበቀስ እየወጣ ጭለማው በብርሃን እየተተካ ሲመጣ አባቴ “በቃ ይኸው ነው እንዴ?” አለ ጮክ ባለ ድምፅ። ሳስበው አባቴ ግርዶሽ ካመጣበት መጥፎ ትዝታ፣ የማይረሳ ጠባሳ እና መለያየት የተነሳ ሳይጠላው አይቀርም። የግርዶሽን ነገር በጣም ቢጠላውም አሁንም ቢሆን ለአያቴ ሲል እና ግርዶሽን ለማየት በሚል ምክንያት ቤተሰብ እና ጓደኞች ስለሚሰባሰቡ በቦታው መገኘቱ አይቀርም። “መቼም ቢሆን ግርዶሽ ሲፈጠር ሳታይ እንዳያመልጥህ። ግርዶሽ ማለት ሁልጊዜም የአንድ ነገር ወይ መጀመሪያ፣ ወይ መጨረሻ ነው። ሁሉም ቤተሰብ ይህንን ክስተት አብሮ ነው መመልከት ያለበት” ይል ነበር አያቴ።

እንደዚህ አይነት የቤተሰብ ስብሰባ በሚኖርበት ጊዜ ሁልጊዜ የሚያረፍደው አጎቴ ቦዴ ነው። ዛሬም አጎቴ ቦዴ እንደለመደው “ምን አመለጠኝ?” ሲል ከየት እንደመጣ ሳናውቅ ሰው ወደተሰበሰበት ጓሮ መጣ። አጎቴ ቦዴ እናቴ ተመልሳ ወደ ቤቷ ለመምጣቷ ትልቁ ምክንያት ነው። እናቴ መቼም ቢሆን ከቤተሰቦቿ እርቃ እንድትጠፋ እና እንድትሄድ አጎቴ አይፈቅድላትም። እናቴ ተመልሳ ወደ ቤቷ እንደትመጣ ያደረገው ለኔ እንደሆነ ነው ይህን ሁሉ አመት የሚነግረኝ። እኔ ኝ እንድትመለስ ያደረገው ለእሷም አስቦ እንደሆነ አውቃለው።

የአጎቴን ጥያቄ የሰማው ኦሱፓ “እረ ወድያው ነው ያለፈው” ብሎ መለሰለት።

አጎቴ ቦዴም “ወይኔ አሁንም አመለጠኝ” እያለ እንደተቆጨ ለማስመሰል ተናገረ። “ሰማዩ እኮ ጨልሞ ወዲያውኑ መልሶ በብርሀን ሲተካ፣ እኔ እኮ መንገድ ጀምሬ ነበር” አለ።

አጎቴ ይህን እንደተናገረ አያቴ እያለፈች ካለችው ጨረቃ ላይ አይኑን ሳይነቅል ቀበል አድርጎ ወዲያው፣ “ሁልጊዜ መንገድ ላይ ነበርኩ” አለ እንደመቀለድ እያለ።

አያቴ ይህን ተናግሮ እንደጨረሰ ሀሳብ ለማስቀየርም ይመስላል “ግሩም ድንቅ ነገር ነው!” አለች አደል ዝግ ባለ ድምፅ።

“በእርግጥም ድንቅ ነው!” አለ አያቴ በመናደድ ስሜት ውስጥ ሆኖ። ወዲያውኑ መነፅሩን አውልቆ በማመንታት መንፈስ ብድግ ብሎ ሄደ። “ቤተሰብ በጋራ ሆኖ ግርዶሽን ማየቱ ወሳኝ ነገር ነው። ደሞ እኮ የምናየው አይናችን እንዳይጎዳ ሸፍነን ነው” አለ። አያቴ ይህን ሲናገር ከኔ ነው የጀመረው። አያቴ እንደተናደደ አውቃለሁ፤ ሆኖም ሲመስለኝ እኔን ሲያየኝ ነው ይህን ለመናገር ያሰበው።

ምናልባት ገብቼ ከነብርኩበት ቅዠት መሰል ሀሳብ ስባንን አይቶኝም ይሆናል እንደዚህ ያለው። አጎቴ ቦዴ የኦሱፓ ትክክለኛ አባት ማን እንደሆነ እንድትነረው አደልን ጠይቋት ሲጨቃጨቁ ሲመለከት ፓፓ ዲ በንዴት በእግሩ ድንጋይ መትቶ የሲቃ ድምፅ ሲያሰማ ሰማሁት። አደል እናቴ ላይ ቂም ያላት ይመስል አፍጥጣ፣ የኔ ትክክለኛ አባት ማን እንደሆነ ስትጠይቃት፣ እናቴ በችኮላ ከአካባቢው ጠፋች። ይህ ሁሉ ውዝግብ ሲፈጠር አባዬ ገና ድሮ መልሱን እንደሚያውቅ ሰው ዝም ብሎ ቆሞ እያየ ነበር። አያቴም በሀኪም የታዘዘለትን መነፅር በእጁ እያሳየኝ፣ “ግርዶሽ ለማየት ሁሉም የቤተሰብ አባላት መነፅር ያስፈልጋቸዋል” ብሎ ነገረኝ።

ወዲያው ኦሱፓ “አሁን ግርዶሹ አልፏል!” ብሎ ሲጮህ ድምፁ በራሴ አለም ፈጥሬ ከነበረው ቅዠት መለሰኝ። ወዲያው ከቅዠቴ ስባንን እንደ ሁልጊዜው እና እንደ ትልቅ ቤተሰብ ሁሉም ሰው በሳቅ ተሞልቶ ተመለከትኩኝ።

← Back to Anthology